የእሁድ ልዩ መረጃ -"IW" የሚባለውን የቪዛ አይነት በተመለከተ
IW የሚባለው የቪዛ አይነት አንድ ሰው ከአሜሪካ ዜጋ ሰው ጋር ጋብቻ ፈጽሞ በትዳር ላይ እያለ የአሜሪካ ዜጋው በአጋጣሚ ህይወቱ ቢያልፍ የሚሰጥ የቪዛ አይነት ነው።
ለዚህ ቪዛ ብቁ ለመሆን ምን ምን መስፈርቶች መሟላት አለበት?
1. የአሜሪካ ዜጋው በሚሞትበት ወቅት ከአሜሪካ ዜጋው ጋር በትዳር ላይ መሆን ያስፈልጋል
2. የአሜሪካ ዜጋው ከሞተ በኋላ ሌላ ትዳር የፈጸመ መሆን የለበትም
3. ፕሮሰሱ የአሜሪካ ዜጋው ከሞት በኋላ ሁለት ዓመት ሳያልፍ መጀመር አለበት
4. ጋብቻው እውነተኛ መሆኑን እና አሜሪካ ለመግባት ብቻ ዓላማ ያልተደረገ መሆን አለበት
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት መስፈርቶች ከተሟሉ ቀጣይ ያለው ሂደት እንደሚከተለው ነው ፡-
ደረጃ 1 -ለአሜሪካ የዜግነትና የስደተኞች አገልግሎት ማእከል (USCIS ) I-360 የሚባል ፎርም ሞልቶ ማስገባት ያስፈልጋል። ይህ ፎርም ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የአሜሪካ ዜጋው በሞተ በ 2 ዓመት ውስጥ መሞላት አለበት።
ደረጃ 2. የትዳር ደጋፊ ሰነዶችን አያይዞ ለአሜሪካ የዜግነትና የስደተኞች አገልግሎት ማእከል (USCIS ) ከI-360 ፎርም ጋር አያይዞ ማስገባት። ከደጋፊ ሰነዶች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ:-
ሟች የትዳር ጓደኛ የአሜሪካ ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሰነዶች (የአሜሪካ ፓስፖርት፣ የዜግነት የምስክር ወረቀት፣ ወይም የአሜሪካ የልደት ሰርተፍኬት)
የጋብቻ የምስክር ወረቀ
የሞት የምስክር ወረቀት
ጋብቻ ትክክለኛ እንደሆነ አማረጋገጫ ልዩ ልዩ ሰነዶች፡ (የጋራ የባንክ ሒሳብ መግለጫዎች፣ የንብረት ሰነዶች፣ ፎቶግራፎች እና የጓደኛ እና ቤተሰብ ማረጋገጫ እማኝነት ደብዳቤዎች ወዘተ)
ማንኛውም ሌላ ተዛማጅ ሰነዶች
ደረጃ 3. ለአሜሪካ የዜግነትና የስደተኞች አገልግሎት ማእከል (USCIS ) ጉዳዩን ገምግሞና አጣርቶ ማጽደቅ ይኖርበታል። ስለዚህም የሚፈጅ ጊዜ አለ።
ደረጃ 4. ፕሮሰሱ በአሜሪካ የዜግነትና የስደተኞች አገልግሎት ማእከል (USCIS ) ከፀደቀ በኋላ ጉዳዩ ወደ አሜሪካ ብሔራዊ የቪዛ ማእከል (NVC) ይላካል። በማዕከሉ የሚፈለጉትን ክፍያዎች መፈጸም የሚያስፈልግ ሲሆን የአመልካቹን የተለያዩ የሲቪል ሰነዶች፣ የፖሊስ የምስክር ወረቀቶች እና ቅጽ DS-260 ይሰበስባል።
ደረጃ 5- የአሜሪካ ብሔራዊ የቪዛ ማእከል ወረፋውን አስጠብቆ ወደ አሜሪካ ኢምባሲ ይልካል በመቀጠልም የአሜሪካ ኤምባሲ በቪዛው ላይ ይወስናል።
ይህ ከላይ የተቀመጠው ሂደት አንድ የአሜሪካ ዜጋ ምንም ዓይነት ፕሮሰስ ሳይጀምር ህይወቱ ካለፈ ሲሆን ፕሮሰሱን አስጀምሮ ህይወቱ ካለፈ ግን ቀጣይ ያለው ሂደት የሚወሰነው ፕሮሰሱ የት ነው ያለው በሚለው ነው ።
1- የአሜሪካ ዜጋ ህይወቱ ያለፈው ፕሮሰሱ USCIS ደረጃ ላይ እያለ ከሆነ ፕሮሰሱ ይቋራጥና አመልካቹ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ I-360 ቅጽ ሞልቶ ፕሮሰሱን እንደገና ያስጀመራል።
2-ነገር ግን የአሜሪካ ዜጋው ህይወቱ ያለፈው ፕሮሰሱ NVC ወይንም ኢምባሲ ደረጃ ላይ ደርሶ ከሆነ ፕሮሰሱ በዛው ይቀጥልና የአሜሪካ ኢምባሲ አስፈላጊ ሰነዶችን አይቶ ውሳኔ ይሰጥበታል።
እንደዚህ አይነት ጉዳይ የገጠመው ሰው ጠበቃ እንዲያማከር ይመከራል።
No comments:
Post a Comment